I admired your spirit I will be surprised if someone did not call you with wrong name (maybe woayne) however Ethiopians politicians as a whole, including the opposition and the government of Ethiopia do not have a guts to find a solutions for the common good. They are incapable of doing that.
They do not care for the next generations but whether they like it or not, Ethiopia will progress with them or without them. History will judge one of these days! Your true Ethiopian spirit will survive forever.
የአሥራ ሰባት አመት ወጣት ነዉ። ጥይት የጎረሰ ሽጉጥ በእጁ ይዟል። እጅግ በጣም ብዙ ሕዝብ በተሰበሰበበት አደባባይ፣ ንግግር አድርገዉ ወደ ጨረሱ አንድ የእድሜ ባለጸጋ ሰዉዬ ቀስ በቀስ ይጠጋል። ሳያስቡት የያዘዉን ሽጉጥ ወደ እርሳቸዉ ደቅኖ ይተኩሳል። ሰውየዉ ይወድቃሉ። አካባቢዉ ተረበሸ። ተናወጠ። አምቡላንስ ተጠርቶ በአፋጣኝ በስፍራዉ ደረሰ። የወደቁትን አባት በአምቡላንሱ የነበሩ የህክምና ባለሞያዎች አነሷቸዉ። የፍጥነት ጉዞ ወደ ሆስፒታል ጀመሩ። ሆስፒታል ሳይደርሱ በመንገድ ላይ የኝህ ሰዉ ሕይወት አለፈች።
ይህ ወጣት ይጋል አሚር ይባላል። ተኩሶ የገደላቸዉም ሰዉ፣ የቀድሞ የእሥራኤል ጠቅላይ ሚኒስተር ይሳቅ ራቢን ነበሩ።
ይሳቅ ራቢን እድሜ ዘመናቸዉን በሙሉ የጥይትና የመድፍ ድምጽ በመስማት ያሳለፉ ጦረኛ ወታደር ነበሩ። በፈረንጆች አቆጣጠር በ1941 ከታዋቂዉ ሞሼ ዳያን ጋር የፓልማክ ግብረኃይል አባል ሆነዉ፣ ያኔ በፍረሳንዮች ቅኝ ግዛት ስር በነበረችዉ በሊባኖስ የናዚ ጀርመን ደጋፊ የነበረዉ የፈረንሳይ ቪቺ መንግስት ወታደሮች ጋር ተዋግተዋል። በዚያ ጦርነት ጊዜ ነበር ሞሼ ዳያን አንድ አይናቸዉን ያጡት።
ከዚያ በኋላ ከአረቦች ጋር በተደረጉት ተከታታይ ጦርነቶች ትልቅ ጀግንነትና የውትድርና ብቃት ያሳዩ፣ በእሥራኤል ታሪክ አሉ ይባሉ ከነበሩት ታላቅ የጦር መሪዎች አንዱ ነበሩ። የእሥራኤል የመከላከያ ሚኒስቴር፣ የጦሩ የኢታ ማጆር ሹም ሆነውም አገልግለዋል።
ይሳቅ ራቢን «እኔ ሰላም ሳላይ እድሜዬን ጨርሻለሁ። ለልጆቻችን ሰላም ማምጣት አለብን» በሚል እምነት፣ ድፍረት የተሞላበት የሰላም እርምጃ ወሰዱ። የእሥራኤል ጠላቶች ከሚባሉ ጋር መነጋገር ጀመሩ።
ኢሳቅ ራቢን ከመገደላቸዉ ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት የተናገሩት፣ ለእኛ ለኢትዮጵያዉያንና ለመሪዎቻችን ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ አስደናቂ አባባል ነበር ። «የሰላም መንገድ ከጦርነት ይሻላል። ይሄን የምለዉ እንደ አንድ ወታደር ነዉ። መከላከያ ሚኒስቴር ሆኜ የእስራኤል ወታደሮች ቤተሰቦች ስቃይ ይሰማኛል። ለነርሱ፣ ለልጆቻችን፣ ለልጅ ልጆቻችን ስንል መንግስታችን ዘላቂ ሰላም እንዲገኝ ማንኛዉንም ቀዳዳ፣ ማንኛዉንም እድል መጠቀም አለበት። ሰላም አንድ ጸሎት ብቻ አይደለም። ሰላም የጸሎታችን መጀመሪያ ነዉ» ነበር ያሉት።
የጦርነትን ፣ የጥላቻና የእልህ ፖለቲካ አደገኛነቱን ያወቁታልና፣ አብረዋቸዉ የነበሩ ጓደኞቻቸዉ ሲረግፉ፣ አካለ ስንኩል ሲሆን፣ ንብረት ሲወድም ፣ ሰዉ በሰዉ ላይ ሲጨክንና አዉሬ ሲሆን አይተዋልና፣ እርሳቸዉ የኖሩበትን በጦርነት የተበከለን አየር ለልጅ ልጆቻቸዉ ማዉረስ አልፈለጉም። እርሳቸዉ ይመኙትና ይናፍቁት የነበረዉን ሰላም፣ እርሳቸዉ ባያገኙትም እንኳን፣ የልጅ ልጆቻቸዉ እንዲያገኙ መደረግ ያለበትን ሁሉ ማድረግ እንዳለባቸዉ ተገነዘቡ። «ለልጅ ልጆቻችን ስንል ሰላም እንዲመጣ የተገኘችዋን ቀዳዳ ሁሉ መጠቀም አለብን» በሚል ጽኑ አምነት፣ በጦርነት ያልሆነ፣ የወስጥና የልብ ጀግንነት ለማሳየት ተንቀሳቀሱ። የእሥራኤል ጠላት ከተባሉት ከነያሲር አራፋት ጋር መነጋገር ጀመሩ።
ብዙ ተቃዉሞ መጣባቸዉ። እነ ናታንያሁ ተነሱባቸዉ። ግትር ፖለቲካ የሚያራምዱ፣ በጭንቅላት ሳይሆን በጠመንጃ የሚያምኑ፣ እነርሱ ብቻ ከሌላዉ እንደተሻሉ አድርገዉ በመቆጠር በትእቢት የተወጠሩ፣ ከነርሱ ዘር ዉጫ ለሌላዉ ግድ የማይሰጣቸዉ ሰዎች በርሳቸዉ ላይ ማንጎራጎር ጀመሩ።
ኢሳቅ ራቢን ግን ወደ ኋላ አላሉም። «የሰላም ጠላቶች አሉ። ሊጎዱን፣ የሰላሙን መንገድ ሊያጨናግፉን የሚፈልጉ። በድፍረት እናገራለሁ። ከፍልስጤማዉያን መካከል የወጣዉ፣ በፊት ጠላታችን የነበረዉ የፍልስጤም ነጻ አውጭ ግንባር አሁን የሰላም አጋራችን ሆኗል» ሲሉ ከቀድሞ ጠላቶቻቸዉ መካከል ወዳጆችን እንዳፈሩ ተናገሩ። ከያሲር አራፋት ጋር በአንድ ላይ ለሰላም ቆሙ። ኢሳቅ ራቢን በጦርነት ሊያጠፉት ያልቻሉትን የያሲር አራፋትን ቡድን በሰላም አሸነፉት።
ታዲያ ለዘመናት በጦር ሜዳ ሲዋጉ በጥይት ያልተመቱት እኝህ ታላቅ ሰዉ፣ በሰላሙ ሜዳ በቴላቪቭ ከተማ ጥይት አገኘቻቸዉ። ለሰላም ለፍቅር ለወንድማማችነት ሲሉ ወደቁ። እጅግ ታሪካዊ፣ ተወዳጅ የሰላም ሰዉ !!!!
የይሳቅ ራቢንን ታሪክ ያለምክንያት አላመጣሁትም። አንዳንዶችን ተቃዋሚዎችን መጨፍለቅ ጀግንነት ይመስለናል። አንዳንዶች ኃይልን የምንመዝነዉ በያዝነዉ ብረትና በዘረጋነዉ የሥለላ አዉታር ነዉ። መነጋገር፣ መወያየት፣ ፍቅርና መግባባት ፣ በጦርነትም ሆነ በጉልበት ከሚገኝ ጊዚያዊ መፍትሄ የበለጠ ዘለቄታ ያለዉ ጥቅም ሊያመጣ እንዲሚችል አናስብም። የሩቁን፣ እኛ ካለፍን በኋላ በልጆቻችንና በልጅ ልጆቻችን ዘመን ሊፈጠር የሚችለዉን፣ ለሁላችንም የሚበጀዉን አንመለከትም። ጊዚያዊ ጥቅማችንንና ስልጣናችን ላይ ብቻ በማተኮር ግትር ፖለቲካ እናራምዳለን።
እንደ ኢሳቅ ራቢን አሁን በሥልጣን ላይ ያሉት የኢሕአዴግ ባለሥልጣናት ከወጣትነታቸዉ ጀምሮ ጦርነትን ያዩ፣ በጦርነት የኖሩ ሰዎች ናቸዉ። በታሪክ ስለሚኖራቸዉ ቦታ፣ ስለ ልጆቻቸዉና የልጅ ልጆቻቸዉ ማሰባ አለባቸዉ እላለሁኝ።
ጸረ-ሽብርተኝነትን ለመቋቋም ተብሎ የወጣዉ አዋጅ ፣ በዚህ አዋጅ መሰረትም፣ ለሰላማዊና ለሕጋዊ ትግል ጠንካራ አቋም ያላቸዉ እነ እስክንደር ነጋን አንዱዋለም አራጌ እንዲሁም ሌሎች በርካታ በሽብር ወንጀል ተከሰዉ ወደ ወህኒ መዉረዳቸዉ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ በተቃዋሚዎች ላይ በየወረዳዉና በየክልሉ የሚደርሰዉ ወከባ … ኢሕአዴግን ከሕዝብ ጋር የሚያጣሉ፣ ጥላቻን እንዲሰፋ የሚያደርጉ፣ ዜጎች የበለጠ ወደ ከረረ አቋም እንዲሄዱ የሚገፋፉ እንጂ፣ ጠቅላይ ሚኒስተር መለስ ዜናዊ አንድ ወቅት እንደ አጀንዳ እንደግፈዋለን ያሉትን የመግባባትንና የእርቅን መንፈስ የሚያመጡ አይደለም።
ተናዶ የኃይል እርምጃ መወሰድ፣ በበቀል መነሳሳት፣ ሰውን ማዋረድ፣ ሰዉን መስደብ፣ ሰዉን መክሰስ በጣም ቀላል ነዉ። በአይናችን ላይ ትልቅ ምሰሶ እያለ የሌላዉን ጉዳፍ ማየት፣ የተገነባዉን ማፍረስ፣ አገርን ከድህነት ወደ ድህነት ማውረድ፣ ጠላቶችን ማፍራት፣ ሕዝብን ከሕዝብ መከፋፈል፣ ወንድምን ከወንድም ማጣላት አስቸጋሪ አይደለም።
ይሳቅ ራቢን እንዳደረጉት ጠላት የነበሩትን ወዳጅ ማድረግ፣ የፈረሰዉን መገንባት፣ አገርን ከድህነት ማውጣት፣ ችግሮችን በዉይይት መፍታት፣ የተጣሉትን ማስታረቅ፣ የተበተኑትን መሰብሰብ፣ ትችትና ወቀሳን በትህትና ተቀብሎ ስድብና አሉባልታን ደግሞ ንቆ ነገሮችን በትእግስት ማሳለፍ ግን እጅግ በጣም ከባድ ነገር ነዉ።
ስለሆነም አቶ መለስ ዜናዊንና ጓደኞቻቸዉን፣ አሁንም የቀናዉን መንገድ እንዲይዙና ለእርቅና ለብሄራዊ መግባባት መዘጋጀታቸዉን ለማሳየት ተጨባጭ ሥራዎችን ለመሥራት እንዲነሱ ጥሪ እንደወትሮው በደጋሜ አቀርባለሁ። ከነዚህ በነአቶ መለስ መወሰድ አለባቸዉ ከምላቸዉ አበይት ተግባራት መካከል የሚከተሉት ሶስቱን በዋናነት እዘረዝራለሁ፡
1. በአገራችን ዋና ከሚባለዉ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ስብስብ ከሆነዉ፣ ከመድረክ ጋር ፣ ቅንነትና መከባበር ባለመብት መልኩ ቀጥተኛ ውይይት መጀመር፤
2. በሽብርተኝነት ክስ፣ የተከሰሱ ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ የሚያደረጉ ጋዜጠኞችንና የፖለቲካ መሪዎችን ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ መፍታት ( እስክንድር ነጋ፣ አንዱዋለም አራጌ፣ ናትናኤል መኮንን፣ ርዮት አለሙ፣ ዉብሸት ታዬ እንዲሁም ሌሎች….)
3. ሽብርተኛ ተብለዉ የተሰየሙ ድርጅቶች በሙሉ ( ከአልሻባብና ከአልካይዳ በስተቀር) ከሽብርተኝነት መዝገብ ተሰርዘው እነርሱን ወደ ድርድርና ወደ ሰላም ለማምጣት ስትራቴጂዎችን መንደፍ፣ በዚያም ዙሪያ መንቀስቀስ
በአገራችን እርቅና ሰላም እንዲመጣ ማድረጉ የኢሕአዴግ ብቻ ሃላፊነት አይደለም። ኢሕአዴግን እንቃወማለን በምንልም ወገኖች በኩል መደረግ ያለበት ቁልፍ ጉዳዮች አሉ ብዬ አምናለሁ። ሰላም በአንድ በኩል ብቻ አይደለም። እኛ «ኢሕአዴጎች ስልጣን ለመልቀቅ ፈቃደኛ አይደሉም» ብለን እንደምንከሳቸው ሁሉ እነርሱም በበኩላቸዉ «ስልጣን ብንለቅ አይለቁንም፣ በሰላም መኖር አንችልም» የሚል ፍርሃት ሊኖርባቸው ይችላል ብዬ አምናልሁ። በዚህም ምክንያት እርቅ ለመመስረት ፍላጎቱ ቢኖራቸዉም፣ ከፍራቻ የተነሳ፣ በሰላም ስልጣን ከለቀቅን መገደላችን ካልቀረ፣ እስከተቻለን ድረስ ስልጣናችንን ማቆየት አለብን የሚል ድምዳሜ ላይ ሊደርሱ ይችላሉ። ይህ እንግዲህ እርቅ እንዳይመጣ ሁላችንም ወደ ባሰ ደረጃ እንድንደርስ የሚያደርገን ነዉ።
እንግዲህ በዚህ ረገድ የተቃዋሚ ጎራዉ፣ የሰለጠነ፣ ኢትዮጵያውያንን ሁሉ (ኢሕአዴጎችን ጨምሮ) የሚያቀራርብ፣ በበቀልና በጥላቻ ላይ ሳይሆን በፍቅርና በይቅርታ ላይ የተመሰረተ ፖለቲካዎች ማራመድ ይጠበቅበታል።
በቅርቡ ቃሌ በተሰኘዉ የኢትዮጵያዉያን መወያያ መድረክ፣ የፓል ቶክ ስሟ አላማዬ የተባለች አንዲት የተከበረች እህት፣ አንዲት ጥያቄ አቀረበችልኝ። «ወያኔን የኢትዮጵያ ጠላት ነዉ ብለህ ትቀበላለህ ወይ ? » አለችኝ። ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ አትላንታ በተደረገዉ በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያዊያን እግር ኳስ ዉድድር ወቅት፣ የተናገረቸዉን ጠቀስኩላት። ስላሰሯት፣ ለወራት በጨለማ ቤት ዉስጥ ስላስቀመጧት ስለ ኢሕአዴጎች ወ/ት ብርቱካን ስትናገር «ወንድሜ ስመ ጥፉ፣ ግብረ ጥፉ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ምንም ማድረግ አልችልም ወንድሜ ነው» ነበር ያላችዉ።
አንጋፋዉ አርቲስትስ ቴዲ አፍሮ እንዲህ ሲል ከሰባት አመታት በፊት ያቀነቀነዉ ልጥቀስ፡
“ይቅር በለውና የበደለን ወቅሰህ፣ ምህረት አስተምረን አንድ አርገን መልሰህ
ዘጸዓት ለኢትዮጵያ ወደ ተስፋ ጉዞ፣ ባህር የሚያሻግር አንድ ሙሴ ይዞ
ቅርብ ነው አይርቅም የኢትዮጵያ ትንሳዔ፣ በአንድነት ከገባን የፍቅር ሱባዔ
ፍቅር አጥተን እንጅ በረሃብ የተቀጣን፣ አፈሩ ገራገር ምድሩ መች አሳጣን
ኦሲሳ ኦሲሳ ኦሲሳ ማንዴላ፣ ይቅር አባብሎ እንዳስጣለ ቢላ
በተስፋዋ መሬት እንዲፈጸም ቃሉ፣ ሞፈሩን ያዙና ይቅር ተባባሉ …”
እንግዲህ በፊታችን የፈረንጆች የ2012 ዓ.ም የወንድማማችነት መንፈስ የሚወርሰን፣ የገዢዉ ፓርቲ አመራሮች እና ደጋፊዎቻቸዉ የሚቃወሟቸዉን ሁሉ እንደ ጠላት ማየቱን አቁመዉ ዜጎችን በሙሉ እንደ ወንድም የሚያከብሩበት፣ በአገር ዉስጥም ሆነ ከአገር ዉጭም በተቃዋሚ ጎራ ያለን ሁሉ በይቅርታ መንፈስ ተሞልተን፣ ብርቱካን ሚደቅሳ እንዳለቸው፣ ኢሕአዴጎችን እንደ ወንድሞቻችን የምናይበት ዘመን ያደርግልን። አገራችን ኢትዮጵያ የምትፈወሰው በፍቅር ብቻ ነውና መድህኔ አለም ፍቅሩን ያብዛልን
መልካም አዲስ አመት !
0 comments:
Post a Comment